በጀርመን ሙኒክ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አስተባባሪነት ‘ደግሞ ለዓባይ!’ በሚል መሪ መልዕክት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ላይ ከ15ሺ ዩሮ በላይ ተሰበሰበ።
በፕሮግራሙ ላይ የታደሙት ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ገቢውን ያሰባሰቡት በቦንድ ግዥ፣ በመጽሔት ሽያጭና በስጦታ ነው።
በጀርመን ፍራንክፈርት የኢፌዴሪ ቆንስላ ጄነራል ጽ/ቤት ክቡር ቆንስል ጄኔራል አቶ ፈቃዱ በየነ በመርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት በሚወዷት ሀገራቸው ሥም ተሰብስበው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለመደገፍ በመገኘታቸው ያላቸውን አድናቆት ገልጸው፣ በጀርመን ሙኒክ አከባቢ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮሙኒቲ አባላት በሁሉም ዘርፍ ሀገራቸውን ሲደግፉ የነበሩ መሆናቸውን አውስተዋል። አክለውም ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተለመደ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉና ይህንን ስብስብ ወደ መላው የኢትዮጵያ ቀን በማሳደግ በአንድነት ከሀገራቸው ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በጀርመን ሙኒክ አከባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የቦንድ ግዢውን ሲፈጽሙ እንደተናገሩት በዚህ ታሪካዊ ቀን ሀገራቸውን ለመደገፍ በመገኘታቸው የዜግነት ክብር እንደሚሰማቸው ገልጸው፣ በቀጣይም በሁሉም ዘርፍ ድጋፋቸውን አጠናክረው በመቀጠል ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅር በተግባር እንደሚያሳዩ ተናግረዋል ።