በአውስትራሊያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትን ምክንያት በማድረግ ባካሄዱት የበይነ መረብ ውይይት 14,500 ዶላር አሰባሰቡ።
በአውስትራሊያ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር በውይይቱ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት የህብረታችንና የሉዓላዊነታችን መገለጫ እንዲሁም የአሁኑ ኢትዮጵያዊ ትውልድ ዳግም አድዋ የሆነ ፕሮጀክት መሆኑን አንስተው፣ ሁለተኛ ዙር ሙሌቱ ከውስጥና ከውጭ የገጠሙንን ፈተናዎች ሁሉ ተቋቁመን በማሳካታችን እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። አምባሳደሩ አያይዘውም አውስትራሊያን ጨምሮ በውጭ የሚገኙ የሃገራችን ዳያስፖራ አባላት ከመነሻው ጀምሮ ለግድቡ ግንባታ እያደረጉት ያለው ያልተቋረጠ ድጋፍ በእጅጉ የሚያኮራ መሆኑን በመጥቀስ፣ ፕሮጀክቱ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። ከዚህ በተጨማሪም ከሃገራችን ወቅታዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ባደረጉት ንግግር ከውስጥና ከውጭ ተቀናጅተው ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚሰሩ ኃይሎችን በመመከት ረገድ እየተደረገ ያለውን ርብርብ በተለያየ መንገድ ለመደገፍ ዳያስፖራው እያሳየ ያለውን ተነሳሽነት በማድነቅ በዚህ ረገድ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በወቅቱም ከዚህ በፊት በቦንድ ግዥና በስጦታ ሲደረጉ የቆዩ ድጋፎችን አጠናክሮ ስለማስቀጠል፣ ቃል የተገቡ ድጋፎችን ከኮሙኒቲ አመራሮችና ሌሎች የግብረ ሃይል አባላት ጋር ተቀናጅቶ ስለማሰባሰብ፣ ቦንድ በመግዛትና ስጦታ በመስጠት እንዲሁም ሰርተፊኬቶችን በማግኘት ረገድ የነበሩ ሂደቶችን ስለማሻሻል እንዲሁም የሃብት አሰባሰብ ሂደቱን አመቺና ቀልጣፋ ስለለማድረግ ውይይት ተደርጎ ግንዛቤ ተይዟል።
በመጨረሻም ከዚህ በፊት በአውስትራሊያ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገቢ ከተደረገውና ቃል ከተገባው ድጋፍ በተጨማሪ በእለቱ የ10,500 ዶላር ቦንድ ግዢ እና የ4,000 ዶላር ስጦታ በአጠቃላይ 14,500 ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል ተገብቷል።
በዕለቱ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ታላቁ የኢትዮያ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በስኬት በመከናወኑ የተሰማቸውን ደስታ የሚገልጹ የተለያዩ ግጥሞችና የጥበብ ስራዎች ቀርበዋል።