ክቡር የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው እንዲመጡ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ እንግዶቹን ለመቀበል የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑን የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማል አስታውቀዋል ።
በዚሁ መሰረት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ/Ethiopian origin ID/ የታደሰም ሆነ የአገልግሎት ግዜው ያለፈበት፣ በልዩ ሁኔታ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያለ ቪዛ ወደ ኢትዮጵያ መግባት የሚቻል መሆኑን የገለጸ ሲሆን፣ የታደሰንም ሆነ ግዜው ያለፈበትን መታወቂያ ኤርፖርት በኢሚግሬሽን ካውንተር ላይ ተጓዦች ስለሚጠየቁ መያዝ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በሌላ በኩል የሌላ ሃገር ፓስፖርት የያዙና የትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ /Ethiopian origin ID/ አገልግሎት ለማግኘት የሚፈልጉ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና በውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የፓስፖርት እድሳት አገልግሎት ከፈለጉ አስፈላጊ ሰነዶችን በማዘጋጀት http://xn--www-86o.digitalinvea.com/ ድህረ ገጽ ላይ ማመልከት የሚችሉ ሲሆን፣ ተቋሙ በተለየ መልኩ ከ15 ቀን ባልበለጠ ግዜ ውስጥ ተጓዦች በሞሉት አድራሻ በመላክ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል።
ከዚህ በፊት የትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ ያሌላቸው ደንበኞች የቪዛ አገልግሎት ለማግኘት በ www.evisa.gov.et ድህረ ገጽ ላይ ማመልከት የሚችሉ ሲሆን፣ በሂደቱ ለሚገጥማቸው ማንኛውም ችግሮች support@evisa.gov.et በሚለው የተቋሙ የኢሜል አድራሻ ላይ ጥያቄ ማቅረብ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ጥሪ በተደረገበት የጊዜ ገደብ ውስጥ ወደ ሀገር ቤት ለሚገቡ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የመዳረሻ ቪዛ/on arrival visa/ አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ በኤርፖርት ላይ የሚቆዩትን ግዜና ድካም መቀነስ እንዲቻል በኦንላይን ቀድሞ ቢያመለክቱ የሚበረታታ እንደሆነ መግለጻቸውን አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።
የቪዛ ጥያቄ በተቋሙ ህጋዊ ድህረ ገጽ www.evisa.gov.et ላይ ቢቻ ሲቀርብ አገልግሎቱን የሚሰጥ መሆኑንን ተቋሙ አሳስቧል።
ከዚህ ቀደም በሌሎች ገጾች ላይ ጥያቄ እንደሚቀርብና ተገልጋዮች እንደሚጭበረበሩ መገንዘቡን የገለጸው ተቋሙ እስከአሁን የተደረሰባቸው ገጾች www.ethiopiaevisa.com www.ethiopiaonlinevisa.com እና www.evisaforethiopia.com በመሆናቸው እነዚህ አድራሻዎች የተቋሙ አለመሆናቸውን አስታዉቋል፡፡