‘ከዒድ እስከ ዒድ ወደ ሀገር ቤት’ መርሀ ግብር አካል የሆነውና የሐረሪና የአጎራባች ሕዝቦች አልባሳትና ባሕላዊ ቁሳቁሶችን አውደ ርዕይ በማቅረብ የዘንድሮው የሸዋል ዒድ በሐረር ከተማ በይፋ ተጀመረ፡፡
የሀረሪ ክልል ርዕሠ መሥተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪና የኢፌዴሪ ባህልና ስፓርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ በጋራ በመሆን አውደ ርዕዩን የከፈቱት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ እና ከዒድ እስከ ዒድ ወደ ሀገር ቤት ብሔራዊ ጥምር ኮሚቴ ሰብሳቢ ዑስታዝ አቡበክር አሕመድን ጨምሮ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የአጎራባች ሕዝቦች ተወካዮች ተገኝተዋል።
የአውደ ርዕዩን መከፈት ተከትሎም የሸዋል ኢድ ታሪካዊ አመጣጥን በተመለከተ በአቶ አዩብ አብዱላሂ አጭር ጥናታዊ ጽሑፍ የቀረበ ሲሆን፣ በባህላዊ ሁነቱ አንድምታዎች ላይ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
መርሀ ግብሩ ለሚቀጥሉት ሶስት ቀናት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ታውቋል፡፡