ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የተሳተፉበት ‘ኤችአር 6600’ ረቂቅ ሕግን የሚቃወም ሰልፍ በአሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት ተካሄደ፡፡
ሰልፉ በኮንግረስ የዴሞክራቲክ ፓርቲ (ሜሪላንድ) መሪ ስቴኒ ሆየር ቢሮ ፊት ለፊት የተከናወነ ሲሆን፣ በሰልፉ ላይ በሜሪላንድ የሚኖሩ ትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የግዛቱ የኮንግረስ አመራር ረቂቅ ሕጉን ለሕግ አውጪው አካል እንዳያቀርቡ ጥሪ ማቅረባቸውን ከሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ማህበር የዋሺንግተን ግብረ ኃይል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በሰልፉ ላይ ‘ኤችአር 6600’ ኢትዮጵያንና ኤርትራን እንዲሁም የኢትዮጵያና የአሜሪካን የረጅም ጊዜ ግንኙነት የሚጎዳ በመሆኑ መሰረዝ አለበት የሚሉ መልዕክቶች መተላለፋቸው ተገልጿል። የሰልፋ አስተባባሪዎች ስለ ረቂቅ ሕጉ ጎጂነት የሚያስረዳና ሕጉ ለኮንግረስ እንዳይቀርብ የሚያሳስብ ደብዳቤ ለስቴኒ ሆየር ቢሮ ያስገቡ ሲሆን፣ ከሰልፉ በተጨማሪ በኮንግረስ የዴሞክራት ፓርቲ መሪ ስቴኒ ሆየር ጋር በበይነ መረብ ውይይት ለማድረግ ለነገ ቀጠሮ መያዙን ግብረ ኃይሉ አስታውቋል።
ውይይቱ በሜሪላንድ ግዛት የሚኖሩ ብዙ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች ለኮንግረሱ አመራር ረቂቅ ሕጉን እንደሚቃወሙት ለማሳወቅና በሕጉ ዙሪያ ማብራሪያ ለመስጠት መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተመልክቷል።
የዳያስፖራ ተቋማትና አደረጃጀቶች የኮንግረስ አባላትንና ሴናተሮችን በማነጋጋር፣ ሰላማዊ ሰልፍ በማካሄድ፣ ደብዳቤ በመጻፍና የማህበራዊ ትስስር ገጽ ዘመቻ በማድረግ ‘ኤችአር 6600’ እና ‘ኤስ 3199’ ረቂቅ ሕጎች እንዳይጸድቁ አስፈላጊውን ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ ጥረቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ግብረ ኃይሉ ጥሪውን አቅርቧል።
በአሜሪካ የኮንግረስ አባል ቶም ማሊኖውስኪ (ኒውጀርሲ) ዋና አርቃቂነት፣ በያንግ ኪም (ካሊፎርኒያ)፣ ግሪጎሪ ሚክስ (ኒው ዮርክ)፣ ዴቪድ ሲሲሊን (ሮድ አይላንድስ)፣ ብራድ ሼርማን(ካሊፎርኒያ) እና ማይክል ማካውል (ቴክሳስ) ደጋፊነት የተዘጋጀው ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤችአር 6600 ረቂቅ ሕግ የኮንግረሱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ተወያይቶበት ለኮንግረሱ መምራቱ የሚታወስ ነው ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።