ዳያስፖራው ባህልና ታሪኩን ለልጅ ልጆቹ እንዲያስተምርና ሀገራዊ ሚናውን እንዲወጣ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ ጠየቁ፡፡
‘ከኢድ እስከ ኢድ ወደ ሀገር ቤት’ ጥሪን ተከትሎ በተካሄደ ‘ሸዋልን በሀረር’ መርሀ ግብር የማጠቃለያ ሲምፖዚየም ላይ ነው ይህ የተገለጸው፡፡
በሲምፖዚየሙ ላይ የሐረሪ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች እንዲሁም ዳያስፖራዎች ተሳትፈዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው መልእክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ ስለተሰጣቸው እድል አመስግነው፣ ሸዋልን በሀረር መርሀ ግብር እጅግ ውብ በሆነ መልኩ መካሄዱ የክልሉ መንግስት እና ህዝብ ለነባር ባህል እና ስልጣኔ የሚሰጠትን ትኩረት እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
ሃላፊው አክለውም መርሀ ግብሩ የአጎራባች ክልሎችን ልዩ ውበት ከማንጸባረቁም በላይ ከመላው የሀገራችን ክፍሎች እንዲሁም ከመላው አለም ከዒድ እስከ ዒድ ጥሪን ተቀብለው የመጡ የዳያስፖራ አባላትን ተቀብሎ በማስተናገድ የክልሉ ህዝብ የሚታወቅበትን ፍቅርና እንግዳ አክባሪነት በተግባር ያሳየ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የበርካታ ድልብ ባህልና ስልጣኔ ባለቤት መሆኗንም ጠቅሰው፣ የኢትዮጵያ ባህልና ስልጣኔ ኢትዮጵያን የገነቧት በሁሉም አቅጣጫ ያሉ ህዝቦች ባህልና ስልጣኔ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡ በቅርብ ጊዜ የተመሰረቱ ሀገራት ራሳቸውን ለማስተዋወቅ የሄዱበትን ርቀት አንስተው፣ ጥንታዊ ስልጣኔና ቱባ ባህል ያሏት ሀረር አቅሞቿ በሚገባ ለምተው ለቱሪዝም መስፋፋት እድል እንዲፈጥሩ ሁላችንም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
በመላው አለም የሚኖሩ የክልሉ ዳያስፖራዎች እና ምሁራንም የክልሉን ባህል፣ ታሪክና ስልጣኔ ለልጅ ልጆቻቸው እንዲያስተምሩና ሀገራዊ ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀው፣ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ሙሉ ድጋፍ እንደማይለያቸው አረጋግጠዋል። መርሀ ግብሩ ስኬታማ እንዲሆን የየበኩላቸውን ኃላፊነት የተወጡ አካላትንም በሙሉ አመስግነዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ ሹዋልኢድን በዓለም ቅርስነት የማስመዝገብ ፋይዳ፣ የክልሉ ዕደ ጥበብ ምርቶችን መለያ ስለማዘጋጀት፣ የሐረርና ሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶች ስለነበሯቸው ግንኙነቶች፣ በክልሎች መካከል ቱሪዝምን በዘላቂነት ለማሳደግ መከናወን ስላለበት ስትራቴጂያዊ አጋርነት እንዲሁም በተለያዩ ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡